የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት የ2016 በጀት አመት የስራ አፈፃፀም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አስመልክቶ የተቋሙ ስራ አመራር ከሠራተኞች ጋር ዉይይት አደረጉ

የ60ኛ አመት የምስረታ ክብረ በዓል ኢንስቲትዩቱን በሚገባ ያስተዋወቀና ገፅታውን በገነባ መልኩ በስኬት መጠናቀቁ፣ የስራ አመራሩና የሁሉም ሰራተኛ ተቀናጅቶ መስራት አንድ ማሳያ መሆኑን በመግለጽ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታከለ አባይነህ ለመላው ስራ አመራርና ሰራተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በመቀጠልም ኢንስቲትዩቱ አመታዊና ስትራቴጂክ እቅዱን ለማሳካት፣ምርትና ምርታማነት ላይ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በመፍታት ገቢውን ለማሳደግ እንዲሁም የወደፊት እድገቱን የሚያሳልጡ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የኢንስቲትዩቱን የተፈቀደ ካፒታል ወደ 2.6 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ መፈቀዱ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እቅድ አፈጻጸም ላይ የሚያበረታታ መሆኑ፣ የምምረት አቅምን የሚያጎለብቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶት የተወሰኑት የተጠናቀቁና አብዛኞቹ በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸው፣የገበያ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ዘመናዊ የአመራረት ቴክኖሎጂ እና ጥምር ክትባትቶችን ምርምርና ስርፀት በጥሩ ሂደት ላይ መሆናቸው እንዲሁም በዘርፉ ከተሰማሩ ተፎካካሪ የሆኑ አለምአቀፍ ድርጅቶችን ጋር በጋራ ለመስራት ጥረት እየተደረጉ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ የሰራተኛን የኑሮ ጫና ከመቀነስ ጋር በተያያዘ፣ የመዋቅርና ደሞዝ ስኬል ጥናት በእቀዱ መሰረት እየተከናወነ መሆኑንና ለስራተኛ ድጎማ የሚሆኑ በተቋሙ ውስጥ የአትክልት የማልማት ስራዎች እየተካናወኑ መሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የ2016 በጀት ዓመት የኦፕሬሽናልና የፋይናንስ አፈፃፀም እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ በፕላንና ፕሮግራም አገልግሎት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ አበራ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በአጠቃላይ በ2016 በጀት አመት ኢንስቲትዩቱ ትርፋማነቱን ያስቀጠለ ሲሆን በክትባት ምርት አቅርቦት በዉጭ ሃገር እና በሃገር ዉስጥ ሽያጭ 386.1 ሚሊዮን ብር በማግኘት ካለፈዉ በጀት አመት የ41.6 በመቶ እድገት በማሳየት የእቅዱን 78% ለማሳካት ችሏል፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁ ሲሆን ከፊል ኤስ.ፒ. ኤፍ የዶሮ እንቁላል ማምረቻ ፕላንት ግንባታ እና ዘመናዊ የደረቅ እና ከፊል ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃና ማቃጠያ ጉድጓድ ግንባታ ተጠቃሾች ናቸዉ፡፡

በተለያዩ የኢንስቲትዩቱ የስራ እንቅስቃሴዎች ላይ ከሰራተኞች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በአመራሩ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በአጠቃላይ ሠራተኛውና ስራ አመራሩ በ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀም ላይ ያጋጠሙ የዉስጥና ዉጫዊ ችግሮች ላይ ዉይይት በማድረግ ቀጣይ የኢንስቲትዩን አፈፃፀም የተሻለ ለማድረግና ለተሻለ ስኬት ሁሉም የበኩሉን እንደሚወጣ የጋራ ግንዛቤ ላይ ተደርሷል፡፡

በ2017 በጀት አመት እቅድ ላይ በተደረገው ውይይት ስራ አመራሩና ሰራተኛው በእቅዱ ላይ የጋራ ግንዛቤ በመውሰድ ለእቅዱ መሳካት የሚያጋጥሙ ችግሮችን አፋጣኝ መፍትሔ በመስጠት ተናቦ መስራት እንዲሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በሬቻ ባይሳ እንደገለፁት አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በክትባትና መድሐኒት ገበያ ላይ ከፍተኛ ውድድር እየታየ በመሆኑና ወደፊት ኢንስቲትዩቱ የገበያ ተወዳዳሪነቱን ለማስቀጠል የአመራረት ቴክኖሎጂውን ማዘመንና የሰው ኃይል አቅሙን መገንባት አማራጭ የሌለው ስትራቴጂ መሆኑን ተገንዝበን በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በሠራተኛው በኩል ነባራዊ የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ጥያቄ የተነሳ ሲሆን፣ የኢንስቲትዩቱ ስራ አመራር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚመለከተው የተቋሙ የበላይ አመራር ጋር ችግሩን ለማቃለል እየተሰራ ያለዉ የመዋቅር ጥናት ያለበት ደረጃ ለሰራተኛዉ ተገልጿል፡፡

ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ከሰሀራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ትልቁ የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባት ማምረቻ ተቋም ሲሆን በአሁኑ ወቅት 23 የክትባት ዓይነቶችን በማምረት ለሃገር ውስጥና ለውጭ ሃገር ደንበኞች እያቀረበ የሚገኝ ተቋም ነዉ፡፡

                                 ለዘገባው፡- የኢንስቲትዩቱ ህ.ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን

                                                 ሐምሌ 2016 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *