የብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተካሔደ

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩትን እና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ ገመገመ፡፡

የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማው የኦፕሬሽን፣ የፋይናንስ፣ የኮርፖሬት ገቨርናንስ፣ የፕሮጀክት እና የሪፎርም ግቦች አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ሲሆን ፣ ድርጅቶቹ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅዳቸው ደግሞ ከ2013 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ከሚቆይና ካዘጋጁት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ፣ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ከነበራቸው ዕቅድ አፈጻም ፣ድርጅቶቹ ካሉበት ነባራዊ ሁኔታና ሌሎች መመዘኛ መስፈርቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

በግምገማው ብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ትርፋማነቱን ማስቀጠል እንደቻለ ታይቷል፡፡በበጀት ዓመቱ ካቀደው የትርፍ ዕቅድ የበለጠ ማከናወኑ፣ ካፒታል ማሻሻ ማድረግ መቻሉ፣ ሂሳቡን ወቅታዊ ማድረጉ፣ የመንግሥት ትርፍ ድርሻን መክፈሉ እንደመልካም ጎን የተጠቀሱጉዳዮች ናቸው፡፡ ኢኒስቲትዩቱ በ2016 ዓ.ም 60ኛ ዓመቱን በደማቅ ሁኔታ ማክበሩና እራሱን ለደንበኛና ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ ያደረገው ተግባርም በመልካም ጎን ታይቷል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የብር 386 ሚሊዮን ሽያጭ ገቢ በማግኘት የብር 178 ሚሊዮን ትርፍ ከታክስ በፊት በማስመዝገብ ትርፋማነቱን እያስቀጠለ ይገኛል፡፡ በበጀት ዓመቱ ካለው ተሰብሳቢ ሂሳብም ብር 128 ሚሊዮን መሰብሰብ ችሏል፡፡ኢንስቲትዩቱ የትርፍ ድርሻ ከሚከፍሉ ድርጅቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱም ብር 48.97 ሚሊዮን ለመንግሥት ገቢ አድርጓል፡፡ የምርት ብክነትን መቀነስ፣ በሽያጭ ገቢ እና በትርፍ ከታክስ በፊት አፈጻጸሙ ካለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት የበለጠ መሻሻሎችን ማስመዝገብ መቻሉም በግምገማው ታይቷል፡፡ የኮርፖሬት ማህበራዊ አገልግሎት ኃላፊነትን ለወጣት በተያዘ ዕቅድ መሰረትም የብር 5.13 ሚሊዮን ድጋፍ ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ማበርከት ችሏል፡፡

በዕለቱ የተገመገመው ሌላው የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ኮርፖሬሽኑ የራስ ኃይል የቢዝነስ ዩኒቶችን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ፈቃድ ወስዶ ወደተግባር መግባት መቻሉ ፣በውስጥ አቅም የሰው ሀብት ለማልማት ያከናወናቸው ተግባራት በበጎ ጎን የታዩ ተግባራት ናቸው፡፡ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ካከናወናቸው ልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተግባራት የብር 79.8 ሚሊዮን ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ በራስ ኃይል ሥራዎችን ለማከናወን ባቀደው ዕቅድ መሰረት የብር 6.6 ሚሊዮን ወጪ ማዳን ችሏል፡፡ ኮርፖሬሽኑ አዳዲስ የቢዝነስ ሀሳቦችን አመንጭቶ ወደተግባር በማስገባት አማራጭ የሥራ መስኮችን ለመፍጠር ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች እንደነበሩ በግምገማው ታይተዋል፡፡

ግምገማውን የመሩት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል ሁለቱም ድርጅቶች በበጀት ዓመቱ ያከናወኗቸውን ተግባራት በማመስገንና እንደተቀጣሪ ሳይሆን እንደዜጋ ለማገልገል ያደረጉትን አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም መሻሻል ያለባቸውን ተግባራት በመጠቆም ድርጅቶቹ በሀገር ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መሰረት አድርገው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

                                                                              ===##==

                               ዘገባዉ፡- የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *